User login

አንድ ብርቱካን ለሁለት

- ፕሮፌሰር መስፍን የአዲሱ አንድነት ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ
"ስብሰባው በአንድነት ስም አልተካሄደም" የአንድነት ም/ሊቀመንበር አቶ አሥራት ጣሴ
". . . የሚሉትም ነገር ከይቅርታ ጋር ውሸት ይመስለኛል" የጠቅላላ ጉባዔው አስተባባሪ

(በኃይሌ ሙሉ)

በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ መሥራች አባላት ስም ባለፈው እሑድ በኮከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ መረጠ፡፡ የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አሥራት ጣሴ በበኩላቸው ስብሰባው በአንድነት ስም እንዲካሄድ አለመፍቀዱን ከአዲስ አበባ አስተዳደር ማረጋገጫ ያገኙ መሆናቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አንድነት ፓርቲ ቀደም ሲል ከአባልነት አስወግጃቸዋለሁ ባላቸው ግለሰቦች አስተባባሪነት ሚያዝያ 10 ቀን 2002 ዓ.ም. የተካሄደው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምን ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ የመረጠ ሲሆን፣ ጠቅላላ ጉባዔው ባወጣው የአቋም መግለጫ አሁን በአመራር ስም የተቀመጡ ግለሰቦች የፓርቲውን ገንዘብና ንብረት በኦዲት አስመርምረው ለተመረጠው አዲስ አመራር እንዲያስረክቡ ወስኗል፡፡

ብሔራዊ ምክር ቤቱ በመተዳደርያ ደንቡ የተጣለበትን ኃላፊነት ያለመወጣቱን፣ የመሥራች ጉባዔውንም ውሳኔዎች ተፈጻሚ ያለማድረጉን፣ በዚህ አድራጎቱም ሥራ አስፈጻሚውና አንዳንድ የአመራር አባላት ከሕግና ሥርዓት ውጪ እንዲሠሩ ያደረገ መሆኑን በመገንዘብ በአዲስ መልክ እንዲዋቀር መደረጉን የገለጸው አዲሱ የእነፕሮፌሰር መስፍን አንድነት ፓርቲ፣ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ለፓርቲው ሕግ ተገዥ ባለመሆን የአሠራር መርሖዎችን የጣሰው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አመራር አባላት የተለወጡ መሆናቸውም አስታውቋል፡፡

በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ስም የወጣው ይሄው የአቋም መግለጫ፣ አመራሩ አንድን ግለሰብ አባል ለማድረግ ሲል ብቻ የፓርቲውን ደንብ ባላከበረ ሁኔታ ፕሮግራሙን መለወጡን አጥብቆ አውግዞ፣ ከዚህ በኋላም ያለጠቅላላ ጉባዔው ይሁንታ የፓርቲው ፕሮግራምና መተዳደርያ ደንብ በማናቸውም የሥልጣን አካላት እንዳይለወጥ ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እስርን በተመለከተም ጉባዔው ባወጣው መግለጫ፣ የወ/ት ብርቱካን ይቅርታ የተነሣውና ለእስር የተዳረገችበት ሁኔታ ሕገ ወጥ መሆኑን ከጠቀሰ በኋላ፣ "የአንድነት አመራር ሊቀመንበራችን በፖሊስ በተጠራችበት ወቅት የራስሽ ጉዳይ ማለቱና ከጎኗ ሊቆም አለመቻሉ፣ የብርቱካንን እስር ለምርጫው ቅድመ ሁኔታ አድርገን አናቀርብም፤ ካሉ በኋላ ፎቶ ግራፏን በመያዝ፣ "ብርቱካን እንድትፈታ መድረክን ምረጡ" እያሉ በስሟ መነገድ ጉባዔተኛውን በእጅጉ አሳዝኗል፡፡ "በግል የድርጊቱ ዋና ተዋናይ የሆኑት አመራሮች ይህንን አሳፋሪ ተግባር ሲፈጽሙ ለማስቆም ጥረት ያላደረገው ብሔራዊ ምክር ቤት ጉባዔውን ተጠያቂ አድርጎታል፤" ብሏል፡፡

በጠቅላላ ጉባዔው ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ጠቅላላ ጉባዔው ኮረሙ ተሟልቶ መካሄዱን ገልጸው፣ በጉዳዩ ላይም ወደ ፊት መግለጫ እንደሚሰጡ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ሕጋዊ ዕውቅና እና ሰርተፍኬት ያለው የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አሥራት ጣሴ በበኩላቸው፣ ከፓርቲው የተባረሩ አባላት በአንድነት ፓርቲ ስም ስብሰባ እንዲያካሂዱ ፈቃድ አለማግኘታቸውን፣ የስብሰባው አስተባባሪዎችም ከአዲስ አበባ አስተዳደር ፈቃድ የወሰዱት፣ "በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ተነሳሽነት የወሰዱ" የሚል መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ አሥራት እንደሚሉት፣ አቶ ሰኢድ ኢብራሂም፣ አቶ ከማል ዳውድ እና አቶ ይልቃል ጌትነት የተባሉ ግለሰቦች፣ "በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት" በሚል ዓርብ እለት የስብሰባ ፈቃድ ያቀረቡትንና አስተዳደሩም በቀረበው ጥያቄ መሠረት በደብዳቤ ቁጥር አ.አ./ከ/ጸ/10/30-4/15 ፈቃድ የሰጠበትን ደብዳቤ የአዲስ አበባ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና የስብሰባ ፈቃድ ክፍል ኃላፊ አቶ ማርቆስ ብዙነህ ለራሳቸው፣ ለዶ/ር ኃይሉ አርአያና ለአቶ አንዱአለም አራጌ ትናንት አስነብበዋቸዋል፡፡

ይሄው አቶ ማርቆስ ያስነበቧቸው የስብሰባ ፈቃድ መጠየቂያ ደብዳቤ፣ ስብሰባው የሚካሄድበት ቦታ፣ ኮከበ ጽባሕ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከቀኑ 2፡00 እስከ 12፡00 ሰዓት መሆኑን፣ የስብሰባው ተሳታፊዎችም "ዓላማውን የሚደግፉ ሰዎች" እንደሚል፣ ከመንግሥት የሚፈለገው ድጋፍ የፖሊስ ጥበቃ መሆኑንና የተሣታፊዎች ብዛትም በግምት እስከ 330 እንደሚደርስ የጠቀሰ መሆኑን የገለጹት አቶ አሥራት፣ የዚሁ ደብዳቤ ግልባጭ ለብሔራዊ መረጃ ደኅንነት አገልግሎት፣ ለፌዴራል ፖሊስ ጽ/ቤት፣ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የተላከ መሆኑን ከዚሁ ደብዳቤ መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡

ምክትል ሊቀመንበሩ እንደሚሉት፣ ከአንድነት ፓርቲ የተባረሩት አባላት "የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራርና አባላት" በሚል ስም ስብሰባ ማካሄድ እንደማይችሉ በመግለጽ፣ አዲስ አበባ አስተዳደር የጻፈላቸውን ደብዳቤም አቶ ማርቆስ አስነብበዋቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የሁለቱም ደብዳቤ ፎቶ ኮፒ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ፣ "ይህ የደብዳቤ ልውውጥ የተደረገው በእኛ (በአስተዳደሩ) እና በእነሱ (የስብሰባ ፈቃድ በጠየቁት ግለሰቦች) መካከል በመሆኑ ለእናንተ ማስነበባችን በቂ ነው፤" በማለት ጥያቄያቸውን ሳይቀበሉት እንደቀሩ ገልጸዋል፡፡

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ አስተባባሪ እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው፣ ጠቅላላ ጉባዔው "የአንድነት መሥራች አባላት" በሚል መካሄዱን ጠቁመው፣ "በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ለመወያየት" በሚል የስብሰባ ፈቃድ ተወስዷል የሚባለውም ፍጹም የሌለ ነገር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም፣ "የሚሉትም ነገር ከይቅርታ ጋር ውሸት ይመስለኛል፤" ብለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ማብራርያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የአዲስ አበባ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና የስብሰባ ፈቃድ ሰጪ ክፍል ኃላፊ አቶ ማርቆስ ብዙነህ፣ የአንድነት ፓርቲን በሚመለከት ያልተጣሩ ነገሮች ስላሉ አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡ ባለፈው እሑድ በኮከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት ስብሰባ ላካሄዱት ወገኖች አስተዳደሩ ፈቃድ የሰጠበትን ደብዳቤ እርሳቸው ለአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት ስለማሳየታቸው ላቀረብንላቸው አጭር ጥያቄም "አላሳየናቸውም፤" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

Source: Ethiopian Reporter

Audio

DW Interview with Ato Yaicob, Ato Seye and Dr. Birhanu
Chapter 10 - From Dictatorship to Democracy
Chapter 9 - From Dictatorship to Democracy
Chapter 8 - From Dictatorship to Democracy
Chapter 7 - From Dictatorship to Democracy
Chapter 6 - From Dictatorship to Democracy
Chapter 5 - From Dictatorship to Democracy
Chapter 4 - From Dictatorship to Democracy
Chapter 3 - From Dictatorship to Democracy
Chapter 2 - From Dictatorship to Democracy

Thoughtful Quotes