አውራምባ ታይምስ (አዲስ አበባ)[Video]፡- አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ከስምንት ወር በፊት ከአባልነት ያሰናበታቸውና እርምጃውን በመቃወም ‹መርህ ይከበር› በሚል ስም ሲንቀሳቀሱ የነበሩት 12 አባላት በትናንትናው ዕለት መታሰራቸውን የቡድኑ ም/ሰብሳቢ አቶ የሽዋስ አሰፋ ለአውራምባ ታይምስ ገለጹ፡፡ [Read the news on PDF]
ባለፈው ሳምንት የመርህ ይከበር ቡድን በአዲስ አበባ-ኮከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ በአንድነት አመራር አባላት ላይ ሹም ሽር ማድረጉና በኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ቦታ ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያምን ም/ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡ ይታወሳል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ፓርቲው ጽህፈት ቤቱን፣ ማህተሙንና ሰርተፊኬቱን ለአዲሱ የመርህ ይከበር አመራር እንዲያስረክብ የሚጠይቅ በፕሮፌሰር መስፍን የተፈረመ ደብዳቤ በመያዝ የቡድኑ አባላት ወደ ፓርቲው ጽህፈት ቤት ሲያመሩ በጽህፈት ቤቱ ውስጥ “በመርህ ይከበር” አባላትና በፓርቲው ጽህፈት ቤት ሰራተኞች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ወደ ግጭትና ድብድብ ማምራቱ ታውቋል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ፕሮፌሰር መስፍንን ጨምሮ 12 አባላት ያሉት የመርህ ይከበር ቡድን አባላት እንደታሰሩ ተገልጿል፡፡
ከእነዚህ አባላት መካከል ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም በዛሬው ዕለት በዋስ እንደተለቀቁ አቶ የሽዋስ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ አውራምባ ታይምስ ያነጋገራቸው ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው በበኩላቸው እርሳቸውን ጨምሮ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ለቂርቆስ ክፍለከተማ ፖሊስ መምሪያ ማመልከታቸውን አምነው ‹‹እኔ እስከማውቀው ድረስ ከፖሊስ ጣቢያዎቹ የተሰጠን ምላሽ ‘የእናንተው አባሎች ስለሆኑ በፖለቲካ ጣልቃ አንገባም’ የሚል ነው›› ብለውናል፡፡ በዚሁ ውዝግብና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ከአውራምባ ታይምስ ጋር ያደረጉትን ቃለምልልሰ በነገው ምሽት ይቀርባል፡፡
- Login to post comments
