By Addis Neger News
የመቀሌ ከተማ አዳራሾች ሥራ በዝቶባቸዋል። በተለምዶ “ሐውልቲ” በመባል የሚጠራው አዳራሽ ደግሞ በታሪኩ እንደ አሁኑ ስብሰባ አስተናግዶ የሚያውቅ አይመስልም። ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል እየተጠራ ወደ “ሐውልቲ” ይገባል፤ይወጣል። ሁሉም ይጎርፋሉ። ወንዶች፤ መምህራን፤ የመንግሥት ሠራተኞች… ሴቶች። ሴት ነጋዴዎች፣ ሴት ተማሪዎች፣ ሴት ጉልት ቸርቻሪዎች… ሴቶች። ለማንኛውም ተሰብሳቢ አንድ መልእክት ይነገረዋል። “የተቃዋሚዎች ደርግነት እና የህወሓት ታዳጊነት” … ከሁለት ሳምንት በፊት “ዐሥርት ሹዐተ ህዳጋ” በተባለ ገበያ የሚሠሩ የጉልት ነጋዴዎች ወደ ሐውልቲ ተጠርተው “ያልተነገሩ ታሪኮች” የሚል ዘጋቢ ፊልም እንዲያዩ ተደርገዋል። ፊልሙ የደርግን አስከፊነት እና የሀውዜንን ጭፍጨፋ የሚያሳይ ነው። የፊልሙ መልእክት “ተቃዋሚ ብትመርጡ የፊልሙ ጭብጥ እውን ይኾናል” የሚል አንድምታ ነበረው።
የሁለት “ወልዱዎች” ወግ
ወንድማማቾች ወደ በርሃ ወጡ። ወጣትነታቸውን ለሚያምኑበት ዓላማ አሳልፈውም ሰጡ። ረዥም፣ አስጨናቂ እና አስፈሪ በነበረውን በዚያ ሰዓት አብረው ነበሩ፤ ሞትን በቅርባቸው እያሸተቱ፤ ድሮ። አሁን ግን ጊዜው ተቀይሯል።
ሁለቱ ወንድማማቾች ጎን ለጎን አይደሉም። ተፋጠዋል።በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን የምርጫ ክልል በሆነችው አክሱም እንደ ባላንጣ እየተያዩ ያሉትን ሁለት የተለያዩ ፓርቲዎችን ወክለው ይወዳደራሉ። ህወሃትን እና አረና-መድረክን። ወንድማማቾቹ አውዓሎም እና አባይ ወልዱ። አውዓሎም ለፓርላማ፤ አባይ ለትግራይ ክልል ምክር ቤት። የሁለቱ ወንድማማቾች ታሪክ የቅርብ ጊዜውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዳገት እና ቁልቁለት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ይመስላል።
ሁለቱም በህወሓት ጉዞ ላይ ተመሳሳይ አሻራ የላቸውም። አውዓሎም በህወሓት ትግል ከወንድማቸው የላቀ ተሰሚነት፣ ተሳትፎ እና ሚና ነበራቸው። በህወሓት የትጥቅ ትግል ጅመራ ዘመን ተዋጊዎችን በማነቃቃት ይወደስ የነበረውን የ“ጋንታ 41” ኦፕሬሽን የመራው አውአሎም ወልዱ ነበር። የአውአሎም ተሳትፎ በወታደራዊ መስክ ብቻ የተገደበ አልነበረም። እስከ ዛሬ ብዙዎችን የሚያነታርከውን “ስትራቴጂያዊ ግባችን የትግራይ ትግሪኝ መንግሥት መመሥረት ነው።” የሚለውን ማኒፌስቶ ከአቶ መለስ ዜናዊ እና አቶ ስብሃት ነጋ ጋራ በመኾን ካረቀቁት ታጋዮች መካካል አንዱ አውዓሎም እንደኾኑ ይታመናል። የፅዮን ማርያም ዝክረ በዐል ላይ፤ጠበል ጻድቅ እየቀማመሱ፤ አክሱም ላይ። በማዕከላዊ ግንባር የነበሩት እነ አረጋዊ በርሔ ከአርቃቂዎቹ ጋራ ከተገናኙ በኋላ በብርቱ ጭቅጭቅ መወገዱ ቢነገርለትም፤ ማኒፌስቶው ዛሬም ድረስ ብዙዎችን የሚያነታርክ ከመኾን አልዳነም።
አሁን አውዓሎም ህወሃት ውስጥ የሉም። በ1993 ዓ.ም ከህወሓት ሦስተኛው ክፍፍል “ሣልሳይ ህንፍሽፍሽ” በኋላ ከተገለሉት አመራሮች አንዱ ኾነዋል። ይኹንና ከህወሓት ከወጡ በኋላ ፖለቲካን ወደ ጎን አልተውትም። “ዐረና ትግራይ ለፍትሕ እና ለሉዐላዊነት” ፓርቲን ከመሠረቱ የቀድሞ የህወሓት ቁልፍ ሰዎች አንዱ ናቸው። በህወሓት ውስጥ እያሉም የመጀመሪያው እና ምናልባትም ብቸኛው በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ኾነው ሲሠሩ ነበር።
በተቃራኒው ወንድማቸው ዐባይ ወልዱ ቀስ በቀስ በትግራይ የህወሓት ፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ጎላ ያለ ስም እና ሚና እየያዙ መጥተዋል። ዐባይ ወልዱ በአክሱም ለትግራይ ምክር ቤት ይወዳደራሉ። የአዲስ ነገር ምንጮች እንደሚናገሩት ቀጣዩ የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር የአቶ አውዓሎም ወልዱ ወንድም ይኾናሉ። አቶ አውዓሎምን ለፓርላማ የሚፎካከሯቸው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የደህንነት እና የጸጥታ አማካሪ አቶ ዐባይ ፀሐዬ ናቸው። ዐባይ ፀሐዬ እንደ ቀድሞው የህወሓት ወሳኙ የፖለቲካ ሰው አይደሉም። ህወሓት ውስጥ ወሳኙ አቶ መለስ ብቻ ከኾኑ ዓመታት ተቆጥረዋል። ነገር ግን የወሳኙ የአቶ መለስ ታማኝ ረዳት እና ከምንጊዜውም በላይ ቅርብ እንደኾኑ ይነገርላቸዋል። ለአቶ መለስ ሥልጣን ቁልፍ የኾነ ሚና ያለው የጸጥታ እና ደኅንነት ጉዳዮች በአቶ ዐባይ ዕይታ ሥር ናቸው። “አቶ ዐባይ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን፣ የደኅንነት ዳይሬክተሩን፣ የፖሊስ ሐላፊዎችን ሰብስቦ ያነጋግራል። አስፈላጊ ሲኾን ይገመግማል” ይላሉ አንድ የአዲስ ነገር ምንጭ። ይህ የአቶ ዐባይ ቁልፍ ሐላፊነት ከቀድሞ የትግል አጋራቸው ከነበሩት ከአቶ አውዓሎም ወልዱ ጋራ አክሱም ውስጥ በሚያደርጉት ፍጥጫ ትርጉም ይኖረዋል። አቶ ዐባይ ከተሸነፉ “ሁሉ በእጃቸው፤ ሁሉ በደጃቸው ነው” ይላሉ፤ ሥልጣናቸው በምርጫው ላይ የሚኖረውን ሚና ሲያብራሩ።
ያም ኾኖ አራተኛው የብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫ “ምርጫ” የሚመስለው በዋናነት በትግራይ ክልል ሲኾን የብዙዎች ትኩረትም ወደ ሰሜን እንዲዞር ኾኗል። ባለፉት 19 ዓመታት በትግራይ የአንድ የህወሓት ድምጽ ብቻ ሲሰማ ኖሯል። ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ክልሎች በላቀ ኹኔታ አንድ ድምጽ ብቻ እንዲሰማባት በጥንቃቄ የታሰበባቸው የዕዝ የፖለቲካ የቁጥጥር መዋቅሮች፣ የማይተኛ የፕሮፓጋንዳ ማሽን፣ ሌሎች የተቃውሞ ሃይሎች ፈፅሞ መንቀሳቅስ የማይችሉበት የፖለቲካ ምህዳር ሲገነባ ሰንብቷል። ለአንዳንድ የፖለቲካ ታዛቢዎች ትግራይ በልዝብ አምባገነን ሥርዓት (Authoritarian Dictatorship) በምትተዳደረው ሰፊዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የምትገኝ ለጠቅላይ/ለፍጹማዊ አምባገነንት (TOTALITERIAN DICTATORSHIP) የቀረበ ሥርዓት የሰፈነባት ደሴት ነች። ህወሓትም ይህ አፋኝ ሥርዐት በትግራይ መንሰራፋቱን የሕልውናው ዋስትና አድርጎ ይወስደዋል። የዘንድሮው የትግራይ ምርጫም የሚከናወነው ለዴሞክራሲዊ ምርጫ ፈጽሞ እንዳይመች ተደርጎ ሲረመረም በከረመው በዚህ አፋኝ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ነው፤ በውጥረት እና በጭንቀት።
አብዛኛዎቹ የህወሓት እና የዐረና/መድረክ አመራር አባላት ወደ ትግራይ ከትመዋል። አቶ ስየ አብርሃ መቀሌ የገቡት የአሜሪካ ጉብኝታቸውን አጠናቀው አዲስ አበባ በገቡ በሁለተኛው ቀን ነው። ሌሎች የዐረና መድረክ የበታች አመራር አባላትም ወደ ክልሉ በጊዜ ገብተው ሥራቸውን ከጀመሩ ቆይተዋል። የህወሓት ካድሬዎችም እረፍት የላቸውም። ብዙ ስብሰባ። እዚያም፤ እዚህም፤…ሀውልቲም።
የ“መጀመሪያው” የትግራይ ምርጫ
ባለፉት ሦስት አገር አቀፍ ምርጫዎች በትግራይ የነበረው ድራማ እጅግ ግልጽ፣ ቀላል እና ጨካኝ ነበር፤ ህወሓት ይወዳደራል፤ ህወሓት ያሸንፋል። የህወሓት ካድሬዎችም ይህን እውነታ ያምኑበታል፤ ከልባቸው። “ለመረጣቸው” ሕዝብ “ድምጹን እና የአመኔታ ድምጽን” እንደሰጣቸው በሙሉ ልብ መልሰው ይነግሩታል። በ1997 ዓ.ም ብቻውን የተወዳደረው ህወሓት ሁሉንም ድምፅ ማግኘቱን ሲገልጽ ነበር። ግንቦት 20 ቀን 1997 ዓ.ም የክልሉ የፕሮፓጋንዳ ሐላፊ አቶ ቴዎድሮስ ሐጎስ በሰማዕታት አዳራሽ በተደረገ አንድ ስብሰባ የትግራይ ሕዝብ በምርጫው ከፍተኛ ድምፅ እንዲሰጣቸው ሲገልጡ በሙሉ ልብ ነበር። አቶ ቴዎድሮስ ብቻ ሳይኾኑ ሌሎቹም የአመራር አባላት ይህን ድል ሲያበስሩ እንጂ በምን ዐይነት የምርጫ ሂደት ድሉን እንደተጎናፀፉ ተናግረው አያውቁም።
በቀደሙት ምርጫዎች ሌሎች ፓርቲዎች ወደ ክልሉ ዝር እንዲሉ አይፈለግም። ቢመጡም እንደልብ ተንቀሳቅሰው የፓርቲ ሥራ ሊሠሩ የሚችሉበት እውነታ አልነበረም። ዋና ተወዳዳሪም፤ አሸናፊም ኾኖ እንዲወጣ የሚፈለገው ህወሓት ብቻ ነው። ህወሓቶች ውስጥ ውስጡን “የትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ከአንድ ፓርቲ በላይ አይችልም፤ መሬቱም አይበቃም” የሚል መፈክር ያቀነቅናሉ።
የህወሓትም ታሪክ ይህን ይመሠክራል። ህወሓት ከደርግ ጋራ ያደርግ በነበረው የትጥቅ ትግል ወደ ላቀ ደረጃ ከማሸጋገሩ በፊት የመጀመሪያ ተግባሩ አድርጎ የወሰደው ትግራይ ውስጥ ይቀናቀኑኛል ያላቸውን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ መግታት ዋና ነበር። ገግሓት፣ ኢዲዩ እና ኢህአፓን የመሳሰሉ ድርጅቶች ትግራይ ላይ እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓል።
ዐረና ትግራይ ለፍትህ እና ለሉዐላዊነት ተመሥርቶ ትግራይ ላይ መሬት መርገጥ ሲጀመር ይህን የህወሓት ታሪክ ጠንቅቀው ያውቃሉ፤ ህወሓት ትግራይ ውስጥ ሌሎችን የማስተናገድ ታሪክ እንደሌለው። ህወሓት ራሱን የትግራይ ሕዝብ ተጠሪ ፓርቲ (vanguard party) አድርጎ ሲወስድ፤ ሲሰሩ፤ እነርሱም የዚያው ፓርቲ ታሪክ ዐቢይ አካል ነበሩ።
በአቶ ቴዎድሮስ ሐጎስ የሚመራው የህወሓት የፕሮፓጋንዳ ማሽን የትግራይ አብዛኛው ነዋሪ ከክልሉ ውጭ ለሚኖሩ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ጥርጣሬ እና ስጋት እንዲያድርበት ሳይታክት ሠርቷል። በትግራይ ሕዝብ ሕልውና ላይ የተቃጡ
እንቅስቃሴዎች አድርጎ የተጠቂነት አስተሳሰብ (siege mentality) አስተሳሰብ እንዲሰፍን ተግቷል። በትግራይ “ቅንጅት” የፖለቲካ ካፒታል እንዳይኖረው ለማድረግ ፕሮፓጋንዳው የጎላ ሚና ነበረው።
ዐረና ትግራይ በክልሉ እግሩን መትከል ሲጀመር “ትግርኛ ተናጋሪ ቅንጅት” የሚል ስም የሰጡት እኝሁ የህወሓት የፕሮፓጋንዳ ሐላፊ አቶ ቴዎድሮስ ሐጎስ ናቸው። ነገር ግን ዐረና/መድረክ በትግራይ መንቀሳቀስ ከጀመረ በሁዋላ በትግራይ ሌሎች ድምፆች መሰማት ይዘዋል። ህወሓት ከዘራው ዘር የተለዩ ድምፆች። የካቲት 23 የተሰማው የአቶ አረጋዊ ገብረ ዮሐንስ ሞት በትግራይ ያለውን ኹኔታ በቅርበት እና በጥንቃቄ የሚታይ የፖለቲካ ምዕራፍ መኾኑን ያረጋገጠ ነበር።
የህወሓት የመጨረሻ ምሽግ
የህወሓት የትግል መነሻ የኾነው የትግራይ ክልል ጠንካራ ድጋፍ የሚያገኝበት ክልል ብቻ አይደለም። የፓርቲው የፖለቲካ ቁማርተኞች እንደመጨረሻ ምሽጋቸው የሚጠቀሙበትም ጭምር ነው። ለአዲስ ነገር ሐሳባቸውን ያካፈሉ አስተያየት ሰጭዎች ህወሓት ይህችን የመጨረሻ ምሽጉን ለመከላከል ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይል ስጋታቸውን ይናገራሉ። ባለፉት 19 ዓመታት የተዘረጉት ልዩ ልዩ የአፈና እና የቁጥጥር መዋቅሮች በትግራይን ፍፁም ስታሊናዊ ሥርዐት መዘርጋቱን ያረጋግጣሉ። አንድ ፓርቲ፣ አንድ ድምፅ፣ አንድ ርዕዮተ ዓለምን ለማስረገጥ የተለያዩ ዘዴዎች ተተግብረዋል። ትግራይ ላይ የተሞከሩ የቁጥጥር ዘዴዎች “ውጤታማነታቸው” እየታየ በሌሎችም ክልሎች ይተገበራሉ። “የአፈና ዋናዋ ቤተ ሙከራ ግን ትግራይ ነች” ይላሉ የውስጥ ታዛቢዎች።
ትግራይን ለህወሓት ሕይወት ብቻ የምትመች ለማድረግ እጅግ ወጤታማ የኾነው ከመንግሥት አመራር ተነሥቶ እስከ ቤተሰብ ደረጃ የሚወርደው የዕዝ የቁጥጥር መዋቅር ነው። ሲጀመር “ልማትን ለማቀላጠፍ” በሚል እሳቤ የተዘረጋው የዕዝ መዋቅር እያንዳንዱን ነዋሪ በቀበሌ፣ በጎጥ እና በሕዋስ ያደራጃል። አንድ ሕዋስ ከአስር እስከ ሃያ አባላትን ያቅፋል።
ከህዋስ ቀጥሎ የሚገኘው በጎጥ የተሰናሰለው አደረጃጀት ነው። የመዋቅሩ አደረጃጀት ዋና ግብ ፓርቲው የህብረተሰቡን እንቅስቃሴ እና አስተሳሰብ በግለሰብ ደረጃ ሳይቀር ለማወቅ እና ለመቆጣጠር እንዲችል ማድረግ ነው። “በአንዱ የሕዋስ አባል ቤት እንግዳ ቢመጣ፣ እንግዳው ማን እንደኾነ፣ ለምን እንደመጣ፣ መቼ እንደሚሄድ” ይጣራል፤ ይበጠራል። ህወሓት በሚቆጣጠረው በዚህ ክልል በጎጥ እና በሕዋስ ደረጃ የሚደረገው ቁጥጥር “እንግዳ ሃሳብ” እንዳይገባ ጠፍንጎ የማያዣ እና የመቆጣጠሪያ መሣርያ ነው። የተለየ ሐሳብ ማንጸባረቅ “ለግምገማ” ይዳርጋል። ህወሓት ይህን መዋቅር በመጠቀም ኅብረተሰቡ የሚሠራውን ብቻ ሳይኾን የሚያስበውን ለማወቅ ጭምር ይመቸዋል።
ነገር ግን መዋቅሩ ብቻ በቂ አይደለም። ወጥ የኾነ አመለካከት ለማስፈን የህዋሓት የፕሮፓጋንዳ ማሽን አይተኛም። ድምፂ ወያኔ፣ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ትግርኛ ፕሮግራም፣ ወይን ጋዜጣ፣ እልፍ አእላፍ ስብሰባዎች ፖሊት ቢሮው የሚያስበውን ያለማቋረጥ ወደ ሕዝቡ ያፈሳሉ። ፍርኀትን ይሰብካሉ። የትግራይ ሕዝብ ብቸኛ አማራጭ “ፓርቲው” እና “ፓርቲው” ስለመኾኑ ሳይታክቱ ይለፍፋሉ። “ትምህክተኞች” ፣ “ጠባቦች” እና “ሻዕቢያ” ሕዝቡን በየጊዜው ለማስፈራራት የሚጠቀሱ “አያ ጅቦዎች” ናቸው። ትግራይን የህወሓት ምሸግ ለማድረግ እና በይፋ የተጠቂነት አስተሳሰብ እንዲራመድ ፕሮፓጋንዳው ጠንክሮ ይሠራል። ለአዲስ ነገር አስተያየት ሰጭዎች የ1997ቱ የአቶ መለስ ዜናዊ እና የአቶ አዲሱ ለገሰ የ”ኢንተርሃምዌይ” ፖለቲካ የዚህ ፕሮፓጋንዳ ቅጣይ ነው። የኢንተርሃምዌ ቅስቀሳ ከየትኛውም አካባቢ በበለጠ ስሜት የነካውም እዚሁ ትግራይ ውስጥ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።
ህወሓት የትግራይን ኅብረተሰብ ሁለንተናዊ ማኅበራዊ መዋቅር በመቀየር፤ እርሱ በሚሻው መንገድ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ነው። እንኳን የተለየ ድምፅ ያለው ተቃዋሚ፤ የተለየ ድምፅ ያላት ወፍ ትውር የማትልበት ትግራይ ለማድረግ።
በተዘጋው በር
በትግራይ የሚደረገው ምርጫ በተለያዩ ምክንያቶች የተወሳሰበ እና ውጥረት የሞላበት ይኾናል። ህወሓት ለዘመናት የትግራይ ብቸኛ ተጠሪ ፓርቲ ኾኖ ኖሯል። ሌሎች ስለ ትግራይ የሚቀናቀኑ ፓርቲዎች በትግራይ ሥር እንዳይሰዱ አድርጓል። በትግራይ የሚደረገው ምርጫ ከዐረና/መድረክ የድርጅት ጥንካሬ በላይ ለረጅም ጊዜያት ሲንከባለሉ የመጡት ሕዝባዊ ቅሬታዎች ዋናዎቹ እና የምርጫውን የድምፅ አሰጣጥ የሚወስኑ ይኾናሉ። ህወሓት በስታሊናዊ ሞዴል በሕዝቡ ፈቃድ የሚተገበር ሳይኾን ከላይ ወደ ታች በመፍሰስ ብቻ በተቃራኒ አቅጣጫ ያለውን ፍላጎት የማያጤን ነው። ይህ ዴሞክራሲን የክልሉ ዐቢይ ጥያቄ አድርጎታል። የኤርትራ ጉዳይ፣ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ጉድለት እና የዴሞክራሲ እጦት የትግራይን መራጭ ልቡ ወደ ተቃዋሚዎች እንዲያዘነብል እና እንዲመርጥ ሊያደርጉ የሚችሉ ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች እንደሚኾኑ ጉዳዩን በቅርበት የሚተከታተሉ የአዲስ ነገር ምንጮች ያስረዳሉ።
በመላው ትግራይ “ህወሓት የቤተ ዘመድ ጉባኤ ኾነ” የሚለውን ስሞታ መስማት አዲስ አይደለም። የፖለቲካ ሥልጣን እና የኢኮኖሚ ጥቅም በተወሰኑ የፓርቲው አባላት እና ዘመዶቻቸው ሥር መኾኑ የፈጠረው ቅሬታ የምርጫውን ክንውኖች ከሚዘውሩት ጉዳዮች አንዱ ነጥብ እንደሚኾን ይታመናል። የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ የህወሓት አመራር አባላት የትግራይን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ምሶሶ በቤተሰብ ደረጃ መቆጣጠራቸው ለብዙዎች ሮሮን አትርፎላቸዋል። ብዙዎች “ትግሉ ለዚህ ነበርን?” ብለው ጠይቀዋል፤ መልስ ባይኖርም። በህወሓት ውስጥ የሚታየው “አውራጃዊነት” የፈጠረው “የተጠቀሙ እና ያልተጠቀሙ” የሚለው አስተሳሰብ የፈጠረው ክፍተት የዚህ ምርጫ አንዱ የውጤት መለያ ምክንያት እንደሚኾን የአዲስ ነገር ምንጮች ይጠቁማሉ።
በወረዳዎቹ የሚወዳደሩ ሰዎች ማንነት እና የኋላ ታሪክ ለምርጫው ውጤት አንዱ አንኳር ነጥብ ነው። ስየ በተንቤን፣ መለስ እና አረጋሽ በአድዋ፤ ዐባይ ፀሐዬ እና አውዓሎም በአክሱም፣ ገብሩ አሥራት እና አዲስዓለም ባሌማ በመቀሌ በሚያደርጓቸው ውድድሮች ከፓርቲዎቹ በላይ የግለሰቦቹ የኋላ ታሪክ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል። አንድ የአዲስ ነገር የትግራይ ምንጭ “አቶ መለስ ከተሸነፉ ጠቅላይ ሚኒስትር መኾን አይችሉም፤ ስለዚህ ሰውየው ውጤቱ ምንም ኾነ ምን አይሸነፉም” ሲሉ ይናገራሉ። ይህ እውነታ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ብቻ የሚመለከት አይደለም። ወይዘሮ አዜብ መስፍን በሚወዳደሩበት በወልቃይትም ተመሳሳይ ገጽታ አለው። የሰሜን ዕዝ ጦር በሚገኝበት ሽሬ ተቃዋሚዎች ቢያሸንፉም፤ ላያሸንፉ የሚችሉበት የምርጫ ወረዳ ነው። “ቦታው የጦርነት ቀጣና ነው። ህወሓት ይህን ቦታ አሳልፎ ሰጥቶ እንቅልፍ አይተኛም።” ይላሉ።
የፖለቲካ ተንታኞች ከምርጫ 97 በኋላ እየጠበበ የመጣውን የፖለቲካ ምህዳር ተከትሎ በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ማሸነፉ የማያጠራጥር፤ የምርጫ ሂደቱንም የይስሙላ ሲሉ ይገልጹታል። ምርጫው ጠንካራ ተቃዋሚ በሌለበት፤ በአንጻሩ የኢሕአዴግ የአፈና እጆች በተንሰራፋበት ምህዳር ውስጥ የሚደረግ ነው። ከምርጫ 97 በኋላ ፓርቲዎች በውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶች ተዳክመዋል፤ ሚዲያውና ሲቪል ማሕበራትም እንዲሁ በተሰመረላቸው የማያላውስ ጠባብ ቀይ መስመር ውስጥ መንቀሳቀስ አልቻሉም። በብዙዎቹ መራቾች እይታ ሌሎቹ ክልሎች ያለው ሁኔታ በ1997 ከተደረገው ምርጫ ጋር ሲነጻጸር እጅግ ፉክክር የሌለበት ነው። በትግራይ ያለው ግን የተለየ ነው። ብዙዎች ቢያንስ በትግራይ የተለዩ “ድንገቴዎች” ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ያስባሉ።
“የትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ከአንድ ፓርቲ በላይ አይችልም” የሚለው ህወሓት ሳይወድ በግድ ሌላ ፓርቲ እንዲያስተናግድ ሊደረግ ይችላል። ይህ ምናልባትም ላለፉት 19 ዓመታት በአንድ ፓርቲ ስትመራ የቆየችው ትግራይ ቢያንስ ከጠቅላይ/ፍጹማዊ አምባገነን ሥርዐት (Totalitarian Dictatorship) ወደ ልዝብ አምባገነን (Authoritarian Dictatorship) አገዛዝ “ሊያሳድጋት” ይችላል። ይህም በዴሞክራሲ ጥያቄ ትግራይን ከሌሎቹ የአገሪቱ ክልሎች ጋራ እኩል ያደርጋታል። ግን ይህም ያለ ዋጋ የሚመጣ አይኾንም።
- Login to post comments
